የሳተላይት ምስሎች ጥራት ባለው መልኩ መረጃ ለሚሹ ተቋማት ተደራሽ እየተደረገ ነው

የሳተላይት ምስሎች ጥራት ባለው መልኩ መረጃ ለሚሹ ተቋማት ተደራሽ እየተደረገ ነው- የስፔስ ሳይንስ እና ጂኦ ስፓሻል ኢንስቲትዩት
*************************
የሳተላይት ምስሎች ጥራት ባለው መልኩ ወደ መረጃነት ተቀይረው መረጃ ለሚሹ የተለያዩ ተቋማት ተደራሽ እየተደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ እና ጂኦ ስፓሻል ኢንስቲትዩት ገለጸ።ከሳተላይት ጥራት ያለው መረጃ መቀበል የሚያስችል የብዝኃ ሳተላይት መረጃ መቀበያ እና መቆጣጠሪያ ጣቢያም ወደ ሥራ መግባቱ ታውቋል።በኢትዮጵያ በሳተላይት ቴክኖሎጂ ዘርፍ ስኬታማ ሥራዎች እየተከወኑ መሆኑን በኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ እና ጂኦ ስፓሻል ኢንስቲትዩት የሳተላይት ልማት እና ኦፕሬሽን ዳይሬክተር መላኩ ሙካ ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ የመጣውን ለውጥ ተከትሎ በዘርፉ የላቀ እመርታ በማሳየት ላይ መሆኗን የሚናገሩት ዳይሬክተሩ፣ ሁለት የመሬት ምልከታ ሳተላይቶችን ወደ ጠፈር መላኳን አስታውሰዋል።በጠፈር ላይ የሚገኙት የኢትዮጵያ ሳተላይቶች ከመሬት በ628 ኪሎ ሜትር ረቀት ላይ በመሆን 13.75 ስፓሻል ሪዞሉሽን የምሥል ጥራት ያለው ምሥል በመላክ ላይ መሆኑን አብራርተዋል።ከመሬት ምልከታ ሳተላይቶቹ የሚላኩት ከፍተኛ ጥራት ያላቸው ምስሎችም መረጃ ለሚሹ ሁሉ በግብአትነት እየዋሉ መሆኑን ጠቁመዋል።
ኢንስቲትዩቱ ከሳተላይት ጥራት ያለው መረጃ መቀበል የሚያስችል የብዝኃ ሳተላይት መረጃ መቀበያ እና መቆጣጠሪያ ጣቢያ በቅርቡ ወደ ሥራ ማስገባቱን ገልጸዋል።ከሳተላይት መረጃን የመቀበል ሥራው ብዙ ወጪ የሚጠይቅ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ መሬት ላይ ሆኖ ከተለያዩ ሳተላይቶች መረጃ መቀበያ ጣቢያው አስፈላጊ ስለመሆኑም አብራርተዋል።እንደ ኢዜአ ዘገባ፣ የብዝኃ ሳተላይት መረጃ መቀበያ እና መቆጣጠሪያ ጣቢያው አምስት እና ከዚያ በላይ ከሆኑ የተለያዩ ዓይነት ሳተላይቶች አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎችን ተቀብሎ በከፍተኛ ጥራት ማስተናገድ የሚችል ነው።የሳተላይት ምሥልን በጥራት ተቀብሎ ለተለያዩ ተግባራት ለማዋል የሚያስችለው መረጃ ተቀባይ ጣቢያ በተለይ ለተፋሰስ እና አጠቃላይ ለግብርና ዘርፍ አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎችን በማቅረብ ላይ ይገኛል ብለዋል።ኢትዮጵያ በታሪኳ የመጀመሪያ የሆነችውን ETRSS-1 የመሬት ምልከታ ሳተላይት ቀጥላም (ET-SMART-RSS) የመሬት ምልከታ ሳተላይት መላኳ ይታወሳል።

Comments are closed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More