የጂኦስፓሻል መረጃ ለዘመናዊ የመሬት አጠቃቀምና አስተዳደር

የጂኦስፓሻል መረጃ ለዘመናዊ የመሬት አጠቃቀምና አስተዳደር

ለአገር ሁለንተናዊ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያላቸው ሁሉም ዓይነት ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ መሠረተ ልማቶች የሚከናወኑት በመሬት ላይ በመሆኑ የጂኦስፓሻል መረጃዎችን በመጠቀም ውጤታማ የመሬት አጠቃቀምና አስተዳደር ሥርዓት መዘርጋት ለአገር ሁለንተናዊ ዕድገት ቁልፍ ሚና ይጫወታል ። በመሆኑም የጂኦስፓሻል መረጃዎችን በመጠቀም መሬትን በአግባቡ መዝግቦ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ለተገቢው ጥቅም ማዋል ለአንድ አገር ኢኮኖሚያዊ ና ማኅበራዊ ዕድገት ውስጥ የማይተካ ድርሻ አለው።
ዘመናዊ የመሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ሥርዓት ካለ በመሬት ላይ የሚካሄዱ የመንገድ ግንባታዎች፣ ሰፋፊ የእርሻ ልማቶች፣ ፣ ለግድቦች፣ ግንባታ፣ ለማዕድን ፍለጋ፣ ለውሃ ልማት የሚሆኑ መሬቶችን ለይቶ ማወቅ ይቻላል። ለእነዚህ ሁሉ የመሬት ላይ ልማቶች ቀዳሚ ግብአት ሆነው የሚያገለግሉት ደግሞ የጂኦስፓሻል መረጃዎች ናቸው። በመሆኑም የጂኦስፓሻል መረጃ ሁለንተናዊ የማሕበረሰብ ዕድገትን ለማፋጠን ለሚደረጉ ጥረቶች መሳካት ዓይነተኛና ወሳኝ ግብዓት ነው። የጂኦስፓሻል መረጃዎች ለመንገድ፣ ለባቡር መስመር፣ ለግድቦች፣ ለልዩ ልዩ ኢንዱስሪዎች ግንባታ፣ ለአውሮፕላን ማረፊያዎች ግንባታ፣ ለጤናና የትምህርት አገልግሎት፣ ለገጠርና ከተማ መሬት ይዞታ (ካዳስተር/ካርታ ሥራ)፣ ለቱሪዝም፣ ለግብርና፣ ለአካባቢ ጥበቃና የተፈጥሮ ሀብት ልማት እጅግ ከፍተኛ ግብዓት ሆነው ያገለግላሉ።
ከኢኮኖሚያዊ ልማትና ዕድገት ባሻገር ለሰዎች የሕይወትና የኑሮ ደረጃ መሻሻል ዋነኛ መሠረት የሆኑት እንደ ትምህርት፣ ጤና፣ የመገናኛ አውታሮችና የኃይል አቅርቦት የመሳሰሉ ሌሎች ሰብዓዊና ማኅበራዊ አገልግሎት የሚሰጡ መሠረተ ልማቶችም የሚከናወኑት መሬት ላይ በመሆኑ የመሬት አጠቃቀምና አስተዳደር ሥርዓትን ማዘመን እጅጉን አስፈላጊ ነው። ይህም ለአንዲት ገር ሰብአዊ ልማትና ማኅበረሰባዊ ዕድገት እጅግ አስፈላጊ በመሆኑ ውስን የሆነውን ውዱን የመሬት ሃብት በአግባቡ ለመጠቀም የሚያስችሉት የጂኦስፓሻል መረጃዎች ፋይዳቸው ከምንም በላይ የላቀ እንዲሆን ያደርገዋል።

ከዚህ በተጨማሪም መሬት ላይ ከሚከናወኑ ሁለንተና ዊ ልማቶች ባሻገር በአሁኑ ሰዓት ዓለም ላይ እየተካሄደ ያለውን የዲጂታላይዜሽን ሥርዓት ግንባታና ይህንን ተከትሎ የተፈጠረውን አዲስ የሳይበር ምህዳር በአዎንታዊ መንገድ ለልማትና ለዕድገት ሊውል በሚችል መልኩ ለመጠቀምም የጂኦስፓሻል መረጃዎች እጅጉን አስፈላጊ ናቸው፡፡ ምክንያቱም ድንበር የለሹንና እጅግ ተለዋዋጭ ባህሪይ የተላበሰውን አዲሱን የሳይበር ምህዳርና የዲጂታል ዓለም በብቃት መጠቀም የሚቻለው ከዘመኑ ጋር የሚራመድ በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ማኅበረሰብ መፍጠር ሲቻል ነው።

ስለሆነም በአሁኑ ሰዓት ዓለም ላይ በሁሉም ዘርፍ ዋነኛ የመወዳደሪያ መድረክ እየሆነ የመጣውን አዲሱን የሳይበር ምህዳር በብቃት ለመጠቀምና ሁለንተናዊ የአገር ልማትና እድገትን ዕውን ለማድረግ መሬትና መሬት ነክ የጂኦስፓሻል መረጃዎችን ከአዲሱ ምናባዊ የዲጅታል ምህዳር ጋር አቀናጅቶ ጥቅም ላይ ማዋል ያስፈልጋል። በእኛም አገርና ሕዝብን ከድህነት አውጥቶ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገሮች ተርታ ለማሰለፍ ወሳኝ በሆኑት ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ልማቶች ውስጥ የጂኦስፓሻል መረጃዎች አስፈላጊነት ከጊዜ ወደጊዜ ፋይዳው እየጎላ መጥቷል።
በአሁኑ ሰዓት እየተካሄደ ካለው ልማት ጋር ተያይዞ የጂኦስፓሻል መረጃ ፍላጎት በከፍተኛ ደረጃ እያደገ መጥቷል።ይህንን ከፍተኛ ፋይዳ ያለውን የመረጃ ግብዓት የማምረትና የማቅረብ ኃላፊነት የተጣለበት የስፔስ ሳንስ እና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩትም በዚህ በኩል የሚፈለገውን አገራዊ የመረጃ ፍላጎት ለማሟላት ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ይገኛል። በአሥር ዓመቱ ብሔራዊ መሪ ዕቅድ በመንግሥት ከፍተኛ ትኩረት የተሰጣቸው የግብርና ኢንቨስትመንት፣ የኢንዱስትሪ ልማት፣ የመንገድ ሥራ፣ የኃይል አቅርቦት፣ የከተማ ልማትና ተመሳሳይ የልማት ዘርፎች የጂኦስፓሻል መረጃን በዋና ግብዓትነት የሚጠቀሙ ናቸው። ስለሆነም የጂኦስፓሻል መረጃ አስፈላጊነት ከምን ጊዜውም በላይ ወሳኝ እየሆነ መጥቷል።
የጂኦስፓሻል መረጃ ለመሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ከፍተኛ ፋይዳ ያለው መረጃ ነው፡፡“ምክንያቱም ውስን የሆነውን የመሬት ሃብት በአግባቡ ለሚፈለገው ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ልማት ማዋል የሚቻለው የመሬት አጠቃቀምና አስተዳደር ሥርዓት ሲኖር ነው። ውጤታማ የመሬት አጠቃቀምና አስተዳደር ሥርዓት መዘርጋትና አሠራሩንም ማዘመን የሚቻለው ደግሞ የጂኦስፓሻል መረጃዎችን በመጠቀም ነው። የጂኦስፓሻል መረጃን በመጠቀም ጥራት ያላቸው የምድር ቅየሳዎችንና የአየር ላይ ፎቶግራፎችን በማምረት እያንዳንዱ የመሬት ሃብት ለተፈለገለት ዓላማ እንዲውል የመሬት አጠቃቀም ካርታዎች ይዘጋጃሉ። ይህም እያንዳንዱ የገጠርና የከተማ መሬት ከሚሰጠው አገልግሎት አኳያ ተለይቶ እንዲመዘገብ ያግዛል። አጠቃላይ የመሬት መረጃዎች በዘመናዊ መንገድ ተመዝገበው እንዲያዙና የመሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ሥርዓቱም ዘመናዊና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል እንዲሆን ያደርገዋል።
በዚህ ረገድ የጂኦስፓሻል መረጃዎችን በመጠቀም መሬትን ከመመዝገብ ጋር በተያያዘ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሰላሳ በመቶ የሚሆነው መሬት የተመዘገበ ሲሆን በምዕራብ አውሮፓ እስከ ዘጠና አምስት በመቶ የሚሆነው መሬታቸው የተመዘገበ መሆኑን መረጃዎች ያመላክታሉ፤ ወደ አፍሪካ ስንመጣ ግን የተመዘገበው መሬት አሥር በመቶ አካባቢ ብቻ ነው። ይህም ከዓለም እጅግ ዝቅተኛው ነው። ከመሬት አጠቃቀምና አስተዳደር ሥርዓት ጋር ተያይዞ በአገራችን ኢትዮጵያ ያለውን ሁኔታ ስንመለከት የመሬት ምዝገባ ሥራው በዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ቢሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን መንግሥት ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ እየተሠራበት ይገኛል።
በመሆኑም መንግሥት ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠቱ በተለይም ከ2004 ዓመተ ምሕረት ጀምሮ ባለፉት አሥር ዓመታት በዘርፉ የተጠናከሩ ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛሉ። በዚህም በአገሪቱ ውስጥ የተጀመሩት የከተማና የገጠር መሬት ምዝገባዎች በሚፈለገው ደረጃ እንዲሳኩ የጂኦስፓሻል ዘርፉ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል። በመሆኑም የጂኦስፓሻል መረጃዎችን የማምረትና የማቅረብ ኃለፊነት የተሰጠው የስፔስ ሳይንስ እና ኦስፓሻል ኢንፎርሜሽን ኢንስቲትዩት እንደ ላይዳር የመሳሰሉ ዘመኑ ያፈራቸውን ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ከፍተኛ ጥራት ያላቸውን የአየር ፎቶግራፎች በማምረት ለመሬት ምዝገባ ሥራው አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶችን የማቅረብ ሥራን ይሠራል።
በዚህም በእስካሁኑ ሂደት ሃምሳ በመቶ ለሚሆነው የአገሪቱ መሬት ምዝገባ የሚሆን የአየር ፎቶግራፍ ተነስቶ የኦርቶሞዛይክ ስራ ተሰርቷል ። ለገጠር መሬት ምዝገባ የሚሆን የአየር ፎቶግራፍና ኦርቶሞዛይክ በአማራ ክልል መቶ በመቶ፣ በደቡብና በኦሮሚያ ክልሎች አርባ በመቶ ተከናውኗል። በተያዘው የበጀት ዓመት ደግሞ በኦሮሚያና በደቡብ ክልሎች የመሬት ምዝገባ ሽፋኑን ለማሳደግ እየተከናወኑ የሚገኙ ሥራዎች አሉ። በቀጣይ በሁሉም ክልሎች የመሬት ምዝገባ ሥራው ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል።
በአጠቃላይ ዘመኑ የደረሰበትን የጂኦስፓሻል ቴክኖሎጂ በመጠቀም የሚመረቱት ከፍተኛ ጥራት ያላቸው የመሬትና መሬት ነክ መረጃዎች የመሬት አጠቃቀምና አስተዳደር ሥርዓት ከተለምዷዊው አሠራር እንዲወጣና እያንዳንዱ የመሬት ሃብት በትክክል ለታለመለት አገልግሎት ብቻ እንዲውል ያስችላል። ከዚህም ባሻገር የጂኦስፓሻል መረጃዎችን በመጠቀም መሬትን መመዝገብና ውጤታማ የመሬት አጠቃቀምና አስተዳደር ሥርዓት መዘርጋ ሌሎች በርካታ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ አንድምታ ያላቸው ዘርፈ ብዙ ፋይዳዎች አሉት።

Comments are closed, but trackbacks and pingbacks are open.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More