ኢንስቲትዩቱ ባዘጋጀው የብሔራዊ ዲጅታል አድራሻ ስርአት ደንብ እና መመሪያ ላይ ውይይት ተካሄደ

መስከረም 26 ቀን2015 ዓ.ም
—————————–

ኢንስቲትዩቱ ባዘጋጀው የብሔራዊ ዲጅታል አድራሻ ስርአት ደንብ እና መመሪያ ላይ በቢሾፍቱ ከተማ ከቁልፍ ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተካሄደ

በእለቱ በተደረገው የምክክር መድረክ ላይ ተገኝተው የመክፈቻ ስነ-ስርአቱን ያስጀመሩት የእለቱ የክብር እንግዳና የኢንስቲትዩቱ ተወካይ አቶ በላቸው ፀሐይ ባደረጉት ንግግር በሀገራችን በየከተሞች ያለውን እድገትና መስፋፋት ተከትሎ ከቦታ ወደ ቦታ ለመንቀሳቀስ በቂ አድራሻ ማግኘት አስቸጋሪ ነው። ሌላው ቀርቶ ችግር ተፈጥሮ ለእርዳታ የሚንቀሳቀሱ የእሳት አደጋ መኪናና ተጎጂዎችን የሚያነሱ አምቦላንሶች ከተጠሩበት ቦታ የሚደርሱት ከብዙ ምሪት በኋላ ነው። ያደጉት ሀገራት ከተሞች የተጠናከረ የአድራሻ ስርዓት ስላላቸው ዘመኑ ያፈራቸው ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ከቦታ ወደ ቦታ በቀላሉ ለመንቀሳቀስ እየተጠቀሙባቸው ይገኛል። በተጨማሪም የየከተማ አስተዳደሮች በከተሞቻቸው ያሉ የማይንቀሳቀሱ ንብረቶችን አድራሻ በመስጠት በቀላሉ ለማስተዳደር እና የማህበረሰባቸውንም የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎች ምቹ እና ወጭ ቆጣቢ ለማድረግ አስችሏቸዋል።
ኢንስቲትዩቱ ህብረተሰቡ የአካባቢውን፣ የመኖሪያ ቤቱን፣ የስራ ቦታውን በቀላሉ ለተገልጋዮች ለመግለጽ፣ የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ ለማግኘት፣ ለወዳጅ ዘመዶቹ እና ለሌሎች አካላት በቀላሉ ያለበትን አድራሻ ለማመላከት ወይም ለመጠቆም የሚያስችል ከሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ ጋር የተጣጣመ እና ዓለም አቀፍ ተሞክሮን መሰረት ባደረገ መልኩ የብሔራዊ ዲጂታል አድራሻ ስርአት ደንብ እና መመሪያ አዘጋጅቶ በዛሬው እለት ከኢንስቲትዩቱ ቁልፍ ባለድርሻ አካላት ጋር ለመወያየት ይህ መድረክ የተዘጋጀ ሲሉ ገልፀዋል፡፡
ከመክፈቻ ስነስርአቱ በመቀጠል የኢንስቲትዩቱ የብሔራዊ ዲጅታል አድራሻ ስርአት አስተባባሪ አቶ አግማሴ ገበየሁ እና የስታንደርድና ጥራት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በሆኑት አቶ እስራኤል ገ/መስቀል የብሔራዊ ዲጅታል አድራሻ ስርአት ደንብ እና መመሪያ ላይ የተዘጋጀው ፅሁፍ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡
የኢንስቲትዩት የዲጂታል አድራሻ ፕሮጀክት ዋና አስተባባሪ አቶ አግማሴ ገበየሁ በእለቱ ባቀረቡት ፅሁፍ በሰጡት ማብራሪያ፤ የዲጂታል አድራሻ ስርዓት መዘርጋት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለው ነው። ግለሰቦች የእለት ከእለት አንቅስቃሴዎቻቸውን ቀላል ከማድረግ ጀምሮ የተቀላጠፈ የመሰረተ ልማት ዝርጋታና ጥገና አገልግሎት ለማግኘት፣ ፈጣን የአስቸኳይ ግዜ እርዳታ እና ቅድመ ማስጠንቀቂያ ለመስጠት፤ መንግስታዊ አገልግሎቶችን ለማዘመን፤ የዲጂታል ኢኮኖሚን ስርዓት ለመዘርጋትና እውን ለማድረግ፤ የኤሌክትሮኒክ ግብይቶችን (e-commerce) እና ማህበራዊ አገልግሎቶችን ለማሳለጥና ለማደገፍ ዋነኛ መሠረት ሆኖ የሚያገለግል ነው። የዲጂታል አድራሻ ስርዓት ማለት መሬት ላይ የሚገኙ ማናቸውንም ነገሮች ህንጻዎች/ቤቶች፣ መንገዶች፣ መሠረተ ልማቶች፣ ክፍት ቦታዎች፣ ፓርኮች፣ መዝናኛና መናፈሻ ቦታዎች እና ሌሎች ነገሮችን መገኛ (location) በካርታ ላይ የማስፈር እና ዜጎች በቀላሉ አድራሻውን እንዲያገኙ በማድረግ የትራንስፖርት ወጪያቸውን እንዲቀንሱና ፈጣን እና ቀልጣፋ አገልግሎት እነዲሰጡ የሚያስችል ስርዓት ነው ።
ይህ ሲተገበርም እያንዳንዱ መሬት ላይ ያለው ነገር ከጀርባው የጂ.ኤን.ኤስ.ኤስ (GNSS በተለምዶ GPS) መረጃ የያዘ የራሱ ልዩ መለያ ቁጥር እንዲኖረው ይደረጋል። በሀገር አቀፍ ደረጃ ወጥ የሆነ አድራሻ ለእያንዳንዱ ቤት፣ መንገድና ሌሎች በመሬት ላይ ያሉ ንብረቶች የሚሰጥበት ስርዓት ነው። ቀደም ባሉት ጊዜያት እንዲሁም አሁንም አብዛኛው ማህበረሰብ የተለያዩ ተቋማትን አገልግሎት ለማግኘት፣ የተለያዩ ግብይቶችን ለመፈጸም፣ ወዳጅ ዘመድ ለመጠየቅ፣ በየመንገዱ እየቆመ እና ሰዎችን እየጠየቀ የሚሄድበት ሁኔታ ያስቀራል ሲሉ ገልፀዋል፡፡
በመጨረሻም ተሳታፊዎች የቀረበውን ፅሁፍ መነሻ በማድረግ በግሩፕ ውይይት ያደረጉ ሲሆን ግልፅ ባልሆኑ ጉዳዮች ላይ ለተነሱ ጥያቄዎች ከመድረክ መልስ ተሰጥቶባቸው ፕሮግራሙ ተጠናቋል፡፡

Comments are closed, but trackbacks and pingbacks are open.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More