ከፊል የጨረቃ ግርዶሽ በኢትዮጵያ

በኢትዮጵያ : ዛሬ ንጋት ከፊል የጨረቃ ግርዶሽ
ሰመራ ዩኒቨርሲቲ ከኢትዮጵያ እስፔስ ሳይንስና ጂኦ ስፓሻል ኢንስቲዩት እንዲሁም እስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ ጋር በመተባበር የጨረቃ ግርዶሽ ትእይንት ለዩኒቨርሲቲዉ ማህበረሰብና ለሠመራና አካባቢ ህብረተሰብ በሠመራ ዩኒቨርስቲ ቅጥር ግቢ ተከናውኗል።
የኢትዮጵያ እስፔስ ሳይንስና ጂኦ እስፓሻል ኢንስቲትዩት የእስፔስ ሳይንስ ተመራማሪ ዶክተር ኤፍሬም በሺር ለኢዜአ እንደገለጹት ክስተቱ መሬት በጸሃይና ጨረቃ መካከል ስትሆን የሚከሰት ነው።
ይህም በተለያዩ ደቡብ አሜሪካና አውሮፓ ሃገራት እንዲሁም ኢትዮጵያን ጨምሮ በተለያዩ የአለማችን ክፍሎች የተከሰተ መሆኑን ገልጸዋል።
በሀገራችንም በተለያዩ አካባቢዎች በከፊል የጨረቃ ግርዶሽ ከንጋቱ 11 ሰአት ጀምሮ ታይቷል ብለዋል።
ከዚህም ውስጥ በአፋር አካባቢ ከንጋቱ 11 ሰአት ጀምሮ ከፊል የጨረቃ ግርዶሹ ሲጀምር በቀላሉ በአይን ሲታይ እንደነበር ገልጸዉ፤በሂደት ጭጋጉ እይታ የሚከለክል ቢሆንም በተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ትእይንቱን መመልከታቸዉን ጠቁመዋል።
ፕሮግራሙ በአፋር የተዘጋጀዉ ህብረተሰቡ ሳይንስ የመጠቀም ባህሉን ለማጎልበትና በአካባቢዉም ከሌሎች አካባቢዎች በተሻለ ለትእይንቱ ያለዉን ምቹ ሁኔታ ታሳቢ በማድረግ ከፊል ግርዶሹን በተሻለ በጥራት ማየት ስለሚቻል መሆኑን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ እስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ ተወካይ አቶ ኪሩቤል መንበሩ በበኩላቸዉ ፕሮግራሙ በአፋር ክልል ሰመራ ዩንቨርስቲ ጋር በመተባበር መዘጋጀቱ ክልሉ መሰል ፕሮግራሞችና እስፔስ ቱሪዝም ያለው ምቹ ተፈጥሯዊ ሁኔታ ለማስተዋወቅ ያግዛል ነው ያሉት።
በተለይም ያለዉ ሜዳማ ሁኔታና ከሌሎች አካባቢዎች በተሻለ በአንጻራዊነት ከጭጋግ የጸዳ ሰማይ እንዲሁም በምሽት ያለዉ ምቹ አየርና ተያያዥ ሁኔታዎች ለእንደዚህ አይነት ትእይንቶች አካባቢዉን ተመራጭ ያደርገዋል።
የሠመራ ዩንቨርስቲ አካዳሚክ ጉዳዩች ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር አብዱሮህማን ከድር እንደገለጹት የጨረቃ ግርዶሽ ትአይንቱ የዩኒቨርስቲዉ ማህበረሰብ በተለይም የዘርፉን ምሁራን በሀገሪቱ በዘርፉ የተሻለ አቅምና እውቀት ካላቸዉ ተመራማሪዎች ጋር መቀራረብና ትብብርን ለመፍጠርም ጭምር ታስቦ የተዘጋጀ ነዉ።

 

እንደዚህ አይነት ፕሮግራሞች በዘርፉም ሆነ በሌሎች የትምህርት መስኮች ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ዶክተር አብዱሮህማን አብራርተዋል።
በተለይም ዩኒቨርሲቲዉ ለእስፔስ ሳይንስ ምርምር ያለውን ምቹ ተፈጥሯዊ ሁኔታ ተጠቅሞ ከእስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲና ከጂኦ-እስፓሻል ኢንስቲትዩት ጋር ጠንካራ ግንኙነት በመፍጠር ክህሎትና ዝንባሌ ላላቸዉ ለተማሪዎችና መምህራን የእዉቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር እንሚያገኙበትን ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር እንደሚሰራም ገልጸዋል። ኢዜአ

Comments are closed, but trackbacks and pingbacks are open.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More