127ኛው የአድዋ ድል በዐል አንጋፋ ምሁራን በተገኙበት በፓናል ውይይትና በባህላዊ ክዋኔ ተከበረ

127ኛው የአድዋ ድል በዐል አንጋፋ ምሁራን በተገኙበት በፓናል ውይይትና በባህላዊ ክዋኔ ተከበረ፦
(“የአድዋ ድል የሁሉም ኢትዮጵያውያን የጋራ ድል ነው፥” /ምሁራን/)
====
127ኛው የአድዋ ድል በዐል በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርና በኢትዮጵያ የስፔስ ሳይንስና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት ትብብር የመንግስት ከፍተኛ አመራሮች፣ ምሁራን ና መላ ሠራተኞች በተገኙበት በፓናል ውይይትና በባህላዊ ክዋኔ በኢንስቲትዩቱ ቅጥር ግቢ ተከብሯል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚንስትር ክቡር በለጠ ሞላ (ፒኤችዲ) ባስተላለፉት መልእክት፥ አድዋ አንድነትን፣ ጽናትን፣ ቁርጠኝነትን፣ በመላበስ የሀገር ፍቅርን፣ ሉዓላዊነትን ማስቀጠልንና መከባበርን ለትውልድ እንድናስተላልፍ እና አዲስ ታሪክ እያስመዘገብን በአብሮነት መዝለቅን የምንዘክርበትና የምናንጸባርቅበት ታላቅ የድል ቀን ነው ።
ክቡር ሚኒስትሩ አክለውም በዐሉ የማይነጥፍ የታሪክ ቅብብሎሽ እያንጸባረቀ እንድናከብረውና ለትውልድ እንድናስተላልፈው አደራው የሁሉም ኢትዮጵያዊ መሆኑን የምንገልጽበት በመሆኑ ታላቅ በዐል ነው ብለዋል።
“ገድለ አድዋ ከመሬት እስከ ሕዋ በቴክኖሎጂ ትሩፋት” በሚል ንዑስ ቃል፤ ተጋባዥ ምሁራን በተገኙበት በተከበረው ልዩ በዓል የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ጂኦስፓሺያል ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዲሳ ይልማ የፓናል መወያያ ጽሑፉን አቅርበዋል።
በበዐሉ ተጋብዘው ከተገኙት አንዱ የሆኑት አንጋፋው ምሁር ዶክተር ዳኛቸው አሰፋ፥ አድዋ የዘመቻ ወቅት የምክክርና የመተማመን ወቅት የነበረና አሁን ካለንበት ወቅት ጋር ብዙ የሚመሳሰል ልምድ የምንቀስምበት የድል ወቅት ነው ብለውታል።
እኛ ኢትዮጵያውያን ጽናት ያነሰን ሰዎች አይደለንም፤ ያሉት ዶክተር ዳኛቸው የሚያለያዩንን ነገሮች አስወግደን በአንድነት መጓዝንና በጽናት ድል ማድረግን ከአድዋ የዘመቻ ወቅት ተምረን እና ቀምረን ለትውልድ ልንገልጽበት የሚያስችለን የድል በዓል ነው ብለዋል ።
በኮተቤ ሜትሮፓሊታን ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት አቶ ኢያሱ በሬንቶ፥ በበኩላቸው
‘ሮናልድ ፕላን’ የተሰኘ የታሪክ ምሁር የጻፈውን ጠቅሰው ባስተላለፉት መልዕክት ታሪክ ልዩ ክስተትን ትፈልጋለች። እንደ አድዋ ያሉ ታሪኮች ደግሞ ክስተቶችን መልሰን ለመመርመር ልዩ እድል ይፈጥሩልናል ብለዋል።
አቶ ኢያሱ አክለውም ከአድዋ የዘመቻና የድል ወቅት በየዘመኑ የገጠሙ ፈተና ሲኖር ለመቋቋም እና በድል ለመዝለቅ የሚያስችል የመማማር እድል ይፈጥራል።
አድዋ፦ የተለያዬ ዳራ ያላቸው ኢትዮጵያዊውያን በምልዐት በአንድነት መዝመታቸው የተረጋገጠበት ዘመቻ ነው። ሁሉም በአንድነት ዘምቷል ሲባል አንድነቱ የስነ ልቦናዊ ትስስርና መተማመን የተገለጸበት ጭምር መሆኑ ሊታወቅ ይገባል። ሁሉም በያለበት ጠላትን የመከተ መሆኑና የድሉ ባለቤት ሁሉም ኢትዮጵያዊ እንደነበረ ሊታመን ይገባል ብለዋል።
በፓናሉ፦ ከአድዋ የተገኙ ትምህርቶች
– ሉዓላዊነትን አስጠብቆ መቆየት
– በመላው ዓለም ለሚገኙ ጥቁሮች የታየ መነቃቃትና የይቻላል ስሜት መፍጠሩ
– በርካታ ትውልደ አፍሪካውያን ወደ አገራቸው እንዲመለሱና የአገራቸውን ሕዝብ ማነቃቃት እንዲችሉ ማነሳሳቱ ወዘተ. የተጠቀሱ ሲሆን፦
በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በሙሉ በይቻላል ስሜት ለአዲስ ትብብር፣ መነሳሳትና ቀጣይ አብሮነት ልንማርባቸው የሚገቡ ቁምነገሮች መሆናቸው ሊታወቅ ይገባል ብለዋል።
አድዋ ከፋፋይ የሆነን ዓላማ መመከት በመቻሉ፣ አፍሪካውያን በተለያዬ ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊዊ ፓለቲካዊ አውድ ቢገጥማቸውም መሻኮትን ተቋቁሞ አንድነትን ማስጠበቅ እና ነጻነትን ማረጋገጥ እንደሚቻል እንደተማሩበት ሁሉ ይህ ትውልድም ሊማርበት ይገባል ብለዋል።
በዐሉ ድል የምንከፋፈልበት ሳይሆን ባለቤትነቱ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ድል መሆኑ ታውቆ፤ የበዐል አከባበሩ ሁሉም ባለቤት በሆነበት፣ በትልቅ አስተውሎት እና ጥንቃቄ በተሞላበት መዘከርና መመራት አለበት።
መንግስት በዚህ ዐመት የጀመረው የተማከለ አከባበር ሊጠናከር እንደሚገባ ተጠቁሞ፤ “በበዐሉ ሰሞን፥ ዘመቻው ሁሉም አንበሳ በነበረበት ዘመንና በሁሉም ተሳትፎ የተከናወነ እንደሆነ ሊመሰከርና ሊነገር ይገባል።” ያሉት ዶክተር ዳኛቸው ድሉን በማውሳት ማሻኮት የመፈለግ አዝማሚያ ከተንኮል የመነጨ አስተሳሰብ ስለሆነ በተገቢው ሊታረምና ልንታገለው ይገባል ብለዋል።
በዐሉ ሲከበርም ዘፈን በቴፕ ሪከርደር ደጋግሞ እያዳመጡ መደሰት እንደመፈለግ ታሪክን በመደጋገም የሚመጣ ፋይዳ ያለ ይመስል የአድዋን ታሪክ በመደጋገም ብቻ ሊሆን አይገባም ያሉት ዶክተር ዳኛቸው፥ የዘመቻውን እና የድሉን ሕያው መንፈስ ለመቀስቀስም ጭምር ነው። እንደ ዶክተር ዳኛቸው የድሉን መንፈስ የምንቀሰቅሰውና የምናስታውሰውና ግድ የሚለን ነገር ሲኖርና በተለይ ትውልዱ አንቀላፍቶ ከተገኘ እና አገር አደጋ ውስጥ ወድቃ በተገኘች ጊዜ ነው። በመሰል ወቅት ከችግሩ ለመውጣትና ለመማር መንፈሱን መቀስቀስ ይገባል ሲሉ በአጽንኦት አሳስበዋል።ገድለ አድዋ ከምድር እስከ ሕዋ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዝማኔ በሚል በተከበረው በዚህ በዐል፥ ኢትዮጵያውያን እንደ ህዝብ እያንዳንዱ ግለሰብ ደግሞ እንደ ዜጋ፦ መማር ያለብን ለመማር እና የሚጠበቅብንን ለመወጣት እለቱን ልንጠቀምበት ይገባል።
አንድ ላይ ስንሆን እንደምንከበር፤ የአድዋ ድል ብዙ ትሩፋት እንዳስገኘልን፥ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት በመዲናችን የተመሰረተው፣ ዓለምአቀፍ ተቋማት ከእኛ ጋር የሆኑት በአንድነት በመዝመታችን የተገኘ ውጤት ነው።
የአድዋን ድል ስናከብር የአንዱን ጥለን የአንዱን አንጠልጥለን ልናከብረው አንችልም። ታሪክን በማሳነስ እና በማንኳሰስም መልክ በማህበራዊ ሚዲያ በሚለቀቁ ሐሰተኛና የተዛቡ ትርክቶች በመነታረክ በዐሉን ፋይዳ ላለማሳነስ ኢትዮጵያዊውያን መጠንቀቅ ይገባልም ብለዋል።
[masterslider id=”8″]

Comments are closed, but trackbacks and pingbacks are open.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More